እየተዳከመ የመጣው የጋብቻ ማሰሪያ
አንዲት ወጣት እናት የሁለት ወር ልጅዋን ታቅፋ ታጠባ ነበር። ከዚያም በድንገት በኃይል በመናደድ ወለሉ ላይ ጣለችው .ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ልጁ ሞተ። እናቲቱም “ባለቤቴ ለቤተሰቡ ግዴለሽ ስለሆነ ልጁን የጣልኩት ሆነ ብዬ ነው” ብላለች። ስለጉዳዩ ከባሏ ጋር በመነጋገር ፋንታ ምንም በማያውቀው ሕፃን ላይ ንዴቷን ተወጣች።
እንዲህ ዓይነት የከፋ እርምጃ የሚወስዱ እናቶች ጥቂት ናቸው። ይሁን እንጂ እንደ እሷ የሚሰማቸው እናቶች ግን ብዙ ናቸው። ባልና ሚስት ጋብቻቸውን የተሳካ ማድረግ ይበልጥ አስቸጋሪ እየሆነባቸው ነው። “ዛሬ በዩናይትድ ስቴትስ እንዳለው ሁሉ ጋብቻን የተሳካ የማድረጉ እድል በጣም ዝቅተኛ ስለሆነ ጠንካራና እዚህ ቀረህ የማይባል የጋብቻ ቃል ኪዳን ውስጥ መግባት አንድ ሙሉ በሙሉ አስተዋይ የሆነ ሰው የማያደርገው አደገኛ ነገር ነው” ሲል ጆርናል ኦፍ ማሬጅ ኤንድ ዘ ፋሚሊ የተባለው መጽሔት ይናገራል።
በዚህ ብጥብጥ በበዛበት ዓለም ውስጥ ያለው የሥነ ምግባር ብልግና፣ አለመጣጣም፣ ዕዳ፣ በአማትና ምራት መካከል ያለው ግጭትና ራስ ወዳድነት በቤት ውስጥ ጠብን ያስነሳሉ። ይህም በተደጋጋሚ ጊዜ ወደ መፋታት ያደርሳል። በጃፓን ውስጥ ነገሩ በጣም አሳሳቢ ከመሆኑ የተነሳ ፍቺን በመቃወም ባላት ጠንካራ አቋም የታወቀችው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እንኳ ፈተው ሌላ የሚያገቡ ሰዎችን ጉዳይ የሚያስተካክል አንድ ልዩ ኮሚቴ ማቋቋም ግድ ሆኖባታል። ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ የቤተ ክርስቲያን ተሳላሚዎች ከፍቺ ጋር በተያያዙ ችግሮች እየተነኩ ነው።
ይሁን እንጂ ፍቺ የችግሩ በጣም ጥቂቱ ክፍል ብቻ ነው። የፍቺ ቁጥር እየጨመረ እንዲሄድ የሚያደርገው የጋብቻ ሕይወት ራሱ እየተዳከመ መሄዱ እንደሆነ በዩናይትድ ስቴትስ የተደረገው ጥናት ያሳያል። ፍቺን ቀላል ከሚያደርጉት ማኅበራዊ ዝንባሌዎች ይልቅ ተጋቢዎቹ ለትዳራቸው ምንም ጥረት ስለማያደርጉለትና የግዴታ ስሜት ስለማይሰማቸው የጋብቻ ኑሮ ድምቀት እየደበዘዘ መጥቷል። ብዙዎች ባልና ሚስት የሚለው ውጫዊ ገጽታ አላቸው። ይሁን እንጂ አብረው አይተኙም። እንዲሁም እርስ በርሳቸው አይነጋገሩም። በሩቅ ምሥራቅ የምትገኝ አንዲት ሴት ‘ከባሌ ጋር በአንድ መቃብር ውስጥ አልቀበርም’ በማለት ለግሏ የመቃብር ጉድጓድ ገዝታለች። አንዳንዶችም እንደ እርሷ ይሰማቸዋል። አሁን ከባሏ ጋር መፋታት ስላልቻለች ከሞቱ በኋላ ለመፋታት ታስባለች። በጣም የሚያሳዝነው እንዲህ ዓይነት ሰዎች ምንም እንኳን ባይፋቱም የጋብቻ ሕይወት የደስታ ምንጭ አልሆነላቸውም።
የኢሳኦ ሁኔታ ይህ ነበር። ሚስቱን ያገባት በድንገት ተነሳስቶ ነበር። ስለዚህ የራስ ወዳድነት የአኗኗር መንገዱን ለመለወጥ አልተገፋፋም። የከባድ መኪና ሹፌር እንደመሆኑ መጠን ጥሩ ገቢ ቢኖረውም የሚያገኘውን ገንዘብ ቤተሰቦቹን ለመንከባከብ ሳይሆን ለራሱ በመብላትና በመጠጣት ያጠፋው ነበር። ከዚህም የተነሳ ዘወትር ከሚስቱ ጋር እንደተጣላ ነው። “የሚያበሳጭ ነገር ሲያጋጥመኝ ቤት እሄድና ንዴቴን በቤተሰቤ ላይ እወጣለሁ” በማለት ያስታውሳል። ዘወትር እረፍት እንደሌለው እሳተ ገሞራ የፍቺ ጉዳይ በየዕለቱ የሚነሳ ነገር ነበር።
ብዙ ወንዶችና ሴቶች መጥፎ ትዳር ችለው ይኖራሉ። ተፋቱም አልተፋቱም ደስታ እያገኙ አይደሉም። ታዲያ ጋብቻቸውን የተሳካ የሚያደርጉበት መንገድ አለን? የጋብቻ ማሰሪያቸውን ለማጠንከር ምን ማድረግ ይቻላል?