ከታሪካዊ ሆስፒታልነት ወደ ልዩ የመንግሥት አዳራሽነት
በ1770 ዝነኛው እንግሊዛዊ አሳሽ የመቶ አለቃ ጄምስ ኩክ 369 ቶን በምትመዝን ኢንዴቨር በተሰኘች መርከብ ያኔ ባልታወቀው የአውስትራሊያ ምሥራቃዊ የባሕር ዳርቻ ጉዞ ጀመረ። ሰኔ 11 ምሽት ላይ መርከቧ በአህጉሩ በስተሰሜን በኩል ራቅ ብሎ በሚገኝ ቦታ ላይ ከአንድ የዛጎል ዓለት ክምር ጋር ተጋጨች። ከዛፍ ግንድ የተሠራው የመርከቢቱ አካል በኃይል ተጎዳ። የመርከቧ ተሣፋሪዎች በሕይወት እንዲተርፉ ከተፈለገ አስቸኳይ ጥገና ያስፈልግ ነበር። በአቅራቢያው የነበረ የአንድ ወንዝ መግቢያ ስድስት ሳምንት የፈጀውን ጥገና ለማድረግ ተስማሚ ቦታ ሆኖ ተገኘ። ከ103 ዓመት በኋላ በዚህ ሥፍራ ወርቅ ተገኘ። የወርቅ ሽሚያ ቀጠለ! በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሀብት ፍለጋ መጡ። ኩክታውን የምትባለው ከተማ ተወለደች።
በ1879 ለሕመምተኞችና ወርቅ ሲያወጡ አደጋ ለሚያጋጥማቸው ሰዎች እንክብካቤ ለማድረግ ቋሚ ሆስፒታል እንዲሠራ የመንግሥት ፈቃድ ተሰጠ። በዚያው ዓመት ሌላው የዓለም ክፍል ሐምሌ 1 የመጀመሪያውን የጽዮን መጠበቂያ ግንብ እትም አየ። ከዚያ ወዲህ ይህ መጽሔት በሚልዮን ለሚቆጠሩ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች የመንፈሳዊ ጤንነት ፕሮግራም ሲያቀርብ ቆይቷል። በዚያን ጊዜ የኩክታውን ሆስፒታል ሕንፃ አንድ ቀን ከዚህ መጽሔት ጋር የቅርብ ቁርኝት ይኖረዋል ብሎ ያሰበ ሰው አልነበረም።
ከመቶ የሚበልጥ ዓመት ካለፈ በኋላ የኩክታውን ሆስፒታል መተኪያ አስፈለገው። አዲስ ሕንፃ ለመሥራት የመንግሥት እርዳታ ተገኝቶ ስለነበር አሮጌውን የሆስፒታል ሕንፃ ለማስወገድ ተጫራቾች ጥሪ ቀረበላቸው። የኩዊንስላንድ ብሔራዊ ድርጅት ለዚህ ታሪካዊ ሕንፃ ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው። ይሁን እንጂ ሕንፃውን ወደ ሌላ ቦታ ማዛወርና ሕንፃውን መልሶ መሥራት በጣም ከፍተኛ ዋጋ የሚጠይቅ ሆነ። ምንም ተጫራች አልቀረበም።
በዚያው ጊዜ አካባቢ በኩክታውን የነበረው የይሖዋ ምሥክሮች አነስተኛ ጉባኤ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን የሚያደርግበት ቋሚ ቦታ እየፈለገ ነበር። መሬት ያልነበራቸው ከመሆኑም በላይ የነበራቸው ገንዘብ 800 የአውስትራሊያ ዶላር ብቻ ነበር። ታዲያ የመንግሥት አዳራሽ ሊሠሩ የሚችሉት እንዴት ይሆን? የጉባኤው ተወካዮች የሆስፒታሉን ሕንፃ ቦታ ለማዛወር ፈቃደኞች ሆኑ፤ ገንዘብ ግን አልሰጡም። ታዲያ ይሖዋ ነገሮችን የሚመራው እንዴት ይሆን? በጣም የሚያስደስት ዜና! ጨረታው ተቀባይነት አገኘ!
አሁን የሚቀጥለው ጉዳይ ለሕንፃው ቦታ ማግኘት ነው። አዎን፣ ሕንፃው እንዳለ የሚጠበቅና እንደነበረ የሚመለስ ከሆነ ነፃ የመንግሥት መሬት ሳይቀርብላቸው እንደማይቀር ተነግሯቸው ነበር። ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮችን በሚጠሉ ማኅበረሰቦች ውስጥ ለታሰበው ፕሮጀክት ተቃውሞ እያየለ መጥቶ ነበር። የምስክሮቹን ዕቅድ ለማጨናገፍ የታለመ አቤቱታም ተዘጋጅቶ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች የኩክታውንን ከተማ ሊቆጣጠሩና ሁሉንም ሆቴሎች ሊዘጉ፣ እንዲሁም ሲጋራ እንዳይሸጥ ሊከለክሉ ነው የሚል ወሬ ተነዝቶ ነበር። እርግጥ ይህ ሁሉ ሐሰት ቢሆንም ክልል መሬትና ሕንፃውን ለመሥራት የሚያስፈልገውን ድጋፍ ማግኘት ይበልጥ አዳጋች እየሆነ መጣ። ሕንፃው እንዲነሳ የተወሰነለት የመጨረሻ ቀን በጣም ቀረበ። የኩዊንስላንድ ግዛት መንግሥት በጉዳዩ ጣልቃ እንዲገባ አስፈላጊ ሆነ። (ከሮሜ 13:2 ጋር አወዳድሩ።) የመንግሥት መሬት ፈቃድ በፍጥነት ተሰጠና የሕንፃው ሥራ ፈቃድ ተሰጠ። መሬቱንና ሕንፃውን በእጃቸው ካደረጉ በኋላ ቀጥሎስ ምን ያደርጉ ይሆን?
በመቶዎች የሚቆጠሩ ምሥክሮች፣ ልምድ ያላቸው የዕደ ጥበብ ባለሙያዎችና ከኩዊንስላንድ ግዛት የተለያዩ ክፍሎች የተውጣጡ የመንግሥት አዳራሾችን በፍጥነት በመሥራት የሠለጠኑ ፈቃደኛ ሠራተኞች ተመዘገቡ። ይህ ፕሮጀክት ልዩ ችግር ነበረው፦ ይኸውም ባለሁለት ፎቅ የሆነውን የሆስፒታሉን ክፍል አንቀሳቅሶ ሕንፃውን እንደገና ማገጣጠምን የሚጠይቅ ነበር። ዝናባማው ወቅት በፍጥነት እየቀረበ ስለነበር ኃይለኛ ዝናብ እያሰጋ ነበር። ሥራው በጊዜ ያልቅ ይሆን? አንዳንድ የከተማው ሰዎች አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበው ነበር። ይሁን እንጂ ለአንዳንዶች የማይቻል የመሰላቸው ነገር ወዲያው ተከናወነ። ሚያዝያ 1986 የሕንፃው ቦታ ተዛውሮ ከዚያም በኋላ ወደ ቀድሞ ክብሩ ተመለሰ።
በኩክታውን አንግሊካን ጋዜጣ ላይ ከሠፈረው አስተያየት በግልጽ እንደታየው ይህ ሁሉ ሥራ ሳይስተዋል አላለፈም። አስተያየቱ በከፊል እንዲህ ይል ነበር፦ “ተግሳፅ እንደሚደርስብኝ ጥርጥር የለውም፣ ይሁንና እስቲ በቤተ ክርስቲያን አካባቢ ተመልከቱና ምን ያህል ባዶ እንደሆነና ሌላውን ቡድን [የይሖዋ ምስክሮች] ደግሞ እዩና ምን ያህል እየሞላ እንዳለ ተመልከቱ። በእንግሊዝ ክርስቲያኖችና በሮማ ካቶሊኮች እየተሞላ ነው። . . . አንድ ድርጅት . . . ትምህርት ቤቱ ስለጠበበው ቤተ ክርስቲያን ብለው ሊጠሩት ወደሚችሉት ሕንፃ ሊለውጡት አሮጌውን ሆስፒታል እንደገዛ አውቃችኋል? . . . ይህ ሁሉ እስኪሆን መፍቀዳችን ምንኛ ደካሞች ነበርን።”
ኩክታውን በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ቱሪስቶች ይጎበኟታል። ያማረ የተፈጥሮ ደን ባለበት ሥፍራና በታላቁ የዓለት ጉብታ ለመደሰትና ስለአካባቢው ታሪክ ለማወቅ ይመጣሉ። አብዛኞቹን ጎብኚዎች የሚስበው የካፕቴን ኩክ ቤተ መዘክር ነው። ከ1989 ወዲህ ታሪካዊው የኩክታውን ሆስፒታልና የይሖዋ ምስክሮች የመንግሥት አዳራሽ በመሆን የሚሰጠው አዲስ ግልጋሎትም ዋናው ጎብኚዎችን የሚስብ ሆኗል። የስጦታ ዕቃ የሚሸጡ መደብሮችም የኩክታውን ሆስፒታል የመንግሥት አዳራሽ ሥዕል የታተመባቸው የሻይ ፎጣዎችና ካናቴራዎችን ይሸጣሉ። ጎብኚዎች በሚመጡባቸው ወቅቶች በየሳምንቱ ከስድስት መቶ እስከ ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ልዩ የሆነውን የ1879 የሕንፃ አሠራር በአካል ተገኝተው ለማየት ሕንፃውን ይጎበኙታል።
አሁን መጠበቂያ ግንብ በመባል የሚታወቀው መጽሔት ለዚያ ቦታ ለሚመጡ ጎብኚዎች በነፃ ይሰጣል። ከ1879 ጀምሮ የዚህ መጽሔት ሥርጭት በየወሩ ሁለት ጊዜ በ111 ቋንቋዎች ከ15 ሚልዮን ቅጂዎች በላይ ወደመሆን አድጓል። እርሱም ከ1914ቱ ትውልድ መካከል አንዳንዶቹ ለሰው ልጆች መልካም አካላዊና መንፈሳዊ ጤንነት ሲመለስላቸው ለማየት እንዲችሉ በሕይወት እንደሚቆዩ ወደሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ያመላክታቸዋል። (ኢሳይያስ 33:24) መላዋ ምድር በሚልዮን በሚቆጠሩ ፈቃደኛ ሠራተኞች አማካኝነት ወደ ገነትነት ትለወጣለች። (መዝሙር 37:29) ታዲያ በአቅራቢያችሁ ያለውን የመንግሥት አዳራሽ ለምን አትጎበኙም? በኩክታውን አካባቢ ከወጣው ወርቅ ሁሉ የሚበልጥ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ነገር ታገኛላችሁ።—ምሳሌ 16:16