የዘመናችን ደግ ሳምራዊ
አንዲት በካናዳ የምትኖር ሴት የመኪና አደጋ ደርሶባት ነበር። አንድ የዘመናችን ደግ ሳምራዊ እርዳታ አደረገላት። (ሉቃስ 10:29–37) ባሳያት ደግነት ልቧ ስለተነካ ዘ ጆርጅታውን ኢንዲፔንደንት ለተባለ ጋዜጣ የሚከተለውን ጻፈች:-
‘ውድ አዘጋጅ:-
‘የጻፍኩት በሁለት ምክንያቶች ነው። በቅድሚያ፣ ባለፈው የሳምንቱ መጨረሻ መኪናዬን መቆጣጠር አቅቶኝ ቦይ ውስጥ በመግባት አደጋ ላይ በወደቅሁ ጊዜ እርዳታ ያደረገልኝን የጆርጅታውን ነዋሪ የሆነውን ሰው ለማመስገን እፈልጋለሁ።
‘አቶ ጆን ሳንደርስ በአካባቢው መኪና እየነዳ ሲያልፍ አየኝና ቆመ። ከዚያም የመጀመሪያ ደረጃ የሕክምና እርዳታ አደረገልኝ። በጣም የሚያጽናና ሰው ነው። አምቡላንስና ፖሊሶች በቦታው እስኪደርሱ ድረስ ከእኔ ጋር ቆይቷል። በማኅበረሰባችሁ ውስጥ እንደ አቶ ሳንደርስ ዓይነት ደግ ሳምራዊ በመኖሩ ማኅበረሰባችሁ ተባርኳል።
‘አቶ ሳንደርስ ደህና መሆኔን ለማረጋገጥ ሲል ባለቤቴንና እኔን ለመጠየቅ ወደ ሆስፒታል መጥቷል። አቶ ሳንደርስ በጆርጅታውን በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና ጽሕፈት ቤት የሚሠራ መሆኑን ሳውቅ በጣም ደነገጥኩ። እነዚህ ሰዎች በመድኃኒት አያምኑም ብዬ አስብ ነበር። የመጀመሪያ ደረጃ የሕክምና እርዳታ ያደረገልኝ ሰው ግን ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ነው። ይህ ደግሞ እንድጽፍ ያነሳሳኝ ሁለተኛው ምክንያት ነው።
‘በሬን ሲያንኳኩ አመናጭቃቸው ስለነበር ሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች ይቅርታ እንዲያደርጉልኝ በትሕትና እጠይቃለሁ። አክራሪዎች ናቸው የሚል እምነት ነበረኝ። አቶ ሳንደርስ ይህ መጥፎ ግምት ስህተት መሆኑን አረጋግጧል። ሁላችሁም ትክክል ነው ብላችሁ ያመናችሁትን ነገር የምታደርጉ ጥሩ ሰዎች ናችሁ።
‘አቶ ሳንደርስ፣ በድጋሚ አመሰግንሃለሁ። በእምነትህ ግፋበት። እግዚአብሔር ይባርክህ።
‘ቲ ኤም፣ ቶሮንቶ’
የይሖዋ ምሥክሮች ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ’ የሚለውን መሠረታዊ ሥርዓት ያምናሉ። (ሉቃስ 10:27) ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የበለጠ ማወቅ የሚፈልጉ ከሆነ ወይም መጽሐፍ ቅዱስን ያለ ክፍያ ለማጥናት ከፈለጉ፣ የይሖዋ ምሥክሮች፣ የፖ.ሣ.ቁ. 5522፣ አዲስ አበባ ብለው ወይም በገጽ 5 ላይ ካሉት አድራሻዎች አመቺ ወደ ሆነው ይጻፉ።